ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን-ቨርጂኒያ ታሪክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን !

እንደሚታወቀው በአሜሪካ በአጠቃላይ በልዩልዩ እስቴቶች በተለይ በዲሲና አካባቢዋ በርካታ አብያተ ክርሲትያናት ተቋቁመው ለምዕመናን ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም መካከል አንዷ በቭርጅኒያ እስቴት በአሌክሳንድሪያ ከተማ የምትገኘው የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፤
የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችው በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ በሆኑት በመላከ ኪዳን ታደሰ ሲሳይና እግዚአብሔር አምላክ በፈቀደላቸው እንዲሁም የኪዳነ ምሕረት ፍቅር ባደረባቸው ምዕመናን እ.ኤ.ዘ አቆጣጠር በየካቲት ወር 1995 ዓ.ም ሲሆን፤ቤተ ክርስቲያኒቱ ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፤ሕግና ቀኖናው በሚያዝ በዘው በቃለ አዋዲው መሰረት በሰበካ ጉባኤ ተደራጅታ በመንፈሣዊውም ሆነ በማኅበራዊው ከፍተኛ አገልግሎት በማበርከት ላይ ትገኛለች፤
ለበርካትታ ሕፃናት በጥምቀት ልጅነት እንዲያገኙ፤እንዲሁም ምዕመናን ጋብቻቸውን በተክሊልና በቅዱስ ቁርባን እንዲፈጽሙ ሰፊ አገልግሎት የምትፈጽም ከመሆኗም በላይ ጠንካራ የሰንበት ት/ቤት ተቋቁሞ ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፤ ከዚሁም ጋር ምዕመናን በመድኃኔ ዓለም፤ በእመቤታችን በቅዱሳን ጻድቃንና ሰማእታት በጽዋ ማኅበራት ስም ተደራጅተው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎታቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፤ ከምታከናውነው መደበኛ አገልግሎት በተጨማሪ በተለይ በጾም ወራት ለሐገርና ለወገን የሚጠቅም የምሕላ ጸሎት ታከናውናለች፤ዘወትር ከምታከናውነው የጸሎት ቅዳሴና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተለየ ምልኩ በየሳምንቱ ሐሙስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ትሰጣለች፤
በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያኒቱ ምንም እንኳ ከተገልጋዩ ምዕመናን አኳያ ሲታይ በቂ ባይሆንም የራሷ የሆነ ቤትና ቦታ ገዝታ አገልግሎቷን በማበርከት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ራሱን የቻለ ሰፊ የሆነ ለክርስቲያን የሚሆን ቤትና ቦታ ለመግዛት በከፍተኛ ጥረት ላይ ትገኛለች፤
ቤተ ክርስቲያን ማለት የማኅበረ ምእመናን ስብስብ ሲሆን በሌላም አነጋገር ክርስቲያኖች የሚሰበሰቡበት ልዩ ስብሐት እግዚአብሔር የሚቀርብበት፤መስዋዕት የሚሰዋበት ልዩ ቦታን ያሳያል፤ እንግዲህ ቤተ ክርስቲያናችንን ስንምለከታት እዝል ቅፅል የሌለባት ቀዳማዊት፤ ሐዋርያዊትና፤ብሔራዊት በክርስቶስ ፤ደም፤በሐዋርያት መሰረት ላይ የታነጸች የተመሰረተች ወልድ ዋሕድ በማለት ፀንታ የኖረች፤የምትኖር ከኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፤
ይህች ጥንታዊት ፤ ሐዋርያዊትና ብሔራዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሐገራችን በመንፈሳዊም ሆነ በማኅበራዊ ከፍተኛ አገልግሎት ከማበርክቷም በላይ ዳር ደንበሩ እሳት መካከሉ ገነት ተብሎ እንዲነገርላት ያደረገች በፍጹም እምነት: ሃይማኖቷን አጥብቃ በመያዝ በምታደርሰው ጸሎትና በምታቀርበው መስዋዕት እንደሆነ በሁላችንም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ግልጽ ነው፤ ሕዝቧም ፤ የባዕድ ሥራዓተ ማህበር መጥቶ የመውደቅ የመነሳት ታሪክ ቢአጋጥመውም በዓለም መድረክ ቢናገር የሚሰማ፤ የሚደመጥ፤ ቢጠይቅ መልስ የሚያገኝ ፤ሐገር አኩሪ፤ ወገን አስከባሪ፤ አገሩን አፍቃሪ ፤ ለወገኑ ተገን ፤ ታላቅ ሕዝብ እንደሆነ ታሪክ ምስክር ነው፤
የእምነት የለሽ ሥራዓት ማህበር ወደ ሐገራችን ተጭኖ ሲገባ የሕዝቦቿን አምልኮታዊ ባሕርይ የሚለወጥ፤ የብዙ ዘመናት ሥራዓትና ወጉን የሚያናጋ፤ ሐገሪቱን የታሪክና የባሕል አልባ በማድረጉ ይህ ታላቅና ኩሩ ሕዝብ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳይወድ በግድ ሀገሩን ልቆ እንዲሰደድ ሆነ በመሆኑም በዓለም ዙሪያ እንደ ጨው ተዘርቶ ይገኛል ፤ይሁን እንጅ በተሰደደበት ቦታ ሁሉ ፤ ባሕላዊ ምግቡን እንጀራ ወጡን፤ ባሕላዊ ልብሱን ጥበብ ኩታውን፤ ሥራዓቱን ወጉንና ሃይማኖቱን በመጠበቅ እንደሚታወቀው ሐገሩንና ባሕሉን በማስተዋወቅ ላይ ሲሆን እምነትን በተመለከተም ‘’በአለህበትና በሄድክበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህን በፍፁም ነብስህ በፍፁም ሐሳብህ በፍፁም ኃይልህ ውደድ ያለውን አምላካዊ ቃል ተግባራዊ በማድረግ በስደቱ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አምልኮተ እግዚአብሔር ለሚፈጸምበት ቅድሚያ በመስጠት ቤተ ክርስቲያናቸውን በመመሥረት እምነታቸውንና ሥራዓተ አምልኮታቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፤

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ  የወደፊት የቤተክርስቲናችን ዕቅዷም የሚከተሉት ናቸው፤

ሰፊ የሆነ ለክርስቲያን የሚሆን ቦታ በመግዛት ቤተክርስቲያኒቷን ከማስፋፋት ጋር፤-
1ኛ.የምግባረ ሰናይ የሴቶች ማኅበር ማቋቋም
2ኛ.የተለያዩ የቤተክርስቲያን የአብነት መምህራንን ማለት የቅዳሴ፤የዜማ፤የቅኔ፤የመጽሕፍት ወዘተ የመሳሰሉትን በማስመጣት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፤ ለወጣቱና ለተተኪው ትውልድ የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ትምህርት እንዲማርና አገሩንም ቤተክርስቲያኒቱንም እንዲያውቅ ማድረግ፤
3ኛ የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት መክፈት
4ኛ የካህናት መኖሪያና የእንግዳ መቀበያ እንዲኖር ማድረግ
5ኛ በእድሜ ፤በሕመም፤ በልዩልዩ ምክንያት እራሳቸውን መርዳት ለማይችሉ ኢትዮጵያውያን መጠለያ እንዲኖር ማድረግ ሲሆን፤ እነዚህን የታቀዱ ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻለው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎና ድጋፍ ሲጨመርበት ስለሆነ ሐብት ያለው በሐብቱ ፤ ሐብቱ የሌለው በጉልበቱ በእውቀቱ ትልቅ ትንሽ ሳይባል በመረዳዳት ለታቀዱ ሥራዎች ተግባራዊነት ሁላችንም እንድንረባረብ በቤተክርስቲያናችን ስም እንጋብዛለን፤

እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላሙን፤አንድነቱንና መግባባቱ ይስጥልን ይህንን የምንኖርበትን ምድረ አሜሪካን በጸጋው በቸርነቱ ይጠብቅልን ለ እኛ ለሁላችንም የአምላካች ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ አሜን